- የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢታዊ ግጥሞች (ክፍል - 11)

72. ሥራቸው ባለጌ አህያ የሚበሉ
ባሕር ወዲያ ማዶ ክፉ ሰዎች አሉ፣
ሐበሻን ለመውረር ሐሳብ ያስባሉ
የኋላ የኋላ መምጣት ይመጣሉ
አምስት ዓመት ገዝተው ወዲያው ይሄዳሉ::
73. ድንጋይ ዱቄት አርገው መንገድ የሚያበጁ
ገመድን ዘርግተው መብራት የሚያበጁ
አህያ የሚያርዱ አሞራ የሚፈጁ
መጡ እየተማሩ ሐበሻን ሊያበጁ
ማማሩን አማረች ግን ብዙ ሰው ፈጁ::
74. እግሩ እንደ ሙቀጫ የሚንከባለል
ቢሄድ አይታክተው አቀበት ቁልቁል
ጭቃ ካለው መንገድ መሄድ የማይችል
ገደል የሚያንሸራትተው የሚንከባለል
ይህንን የገዛ ካለፈው ምንም አይል::
75. በገዛ እጁ ነድፎ ፈትሎ የሚሠራ
ሰውን የሚያስገርም የሚሠራው ሥራ
ልብሱ ተፈላጊ ሰውን የሚያኮራ
ልብሱን ላይሸከሽክ አስተውሎ የሚሠራ
በዚህ አይግረምህ ሌላ አለ የሚሠራ::
76. እፍ ቢሉት አይነድ፣ እፍ ቢሉት አይጠፋ
እንደ እሳት አይጫር ሲበራ ቀልጣፋ
ደጅ ሲበራ የሚያድር በዝናብ አይጠፋ
ሲነቡት የሚገድል ሰውን የሚያጠፋ፣
ነጮች ያበጁታል ሐበሻ ሳይለፋ::
77. የአጼ ምኒልክ ዘር መዓት ወረደባቸው
የቤታቸው አሽከር እንደ ጤፍ ዘራቸው
ጠንካራ ሰው ጠፍቶ ምች አደረቃቸው
ቀብሩ እንዳይታወቅ ሰው እንዳይቀብራቸው
እያሱ እንኳን እንዳይተርፍ በቅናት ፈጃቸው::
78. አልጋው ደኅና ሳለ አሽከር ሳይሰፍርበት
ልጆቹን ቢተካ እንዴት ባማረበት
ሰውም ስይደነግጥ ቀን ሳይጨልምበት
(ሐበሻ በሞላ ሰውም ሳይመክርበት)
እሱም ይኖር ነበር በለዛ በክብረት::
79. የምኒልክ ዘር አልቆ መነን ትቀራለች
ተፈሪን አግብታ ዱቄት ትወልዳለች
ልጆቿም ያልቃሉ እሷም ጉድ ታያለች
የባሏን መከራ ሳታይ ትሞታለች
ሐበሻ የዚያን ቀን ትነፋፍሳለች::
80. መነን ልትሞት ትንሽ ቀን ሲቀር
ሸዋ በተለየ ይሆናል ሽብር፣
አልጋውን ለመያዝ ለመወዳደር
መቼ ይዘገያል የሰው ደም አይቀር
እጃቸው ይያዛል አያገኙም ኸይር::