- የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢታዊ ግጥሞች (ክፍል - 03)

13. ሃምሳ ዓመት ከደመኝ መሐመድ ኑር ዒሳ
መድና ወረቀት ከእጁ ሳይነሣ
ይከትበው ነበረ ዋሪዳው ሲነሣ
የፈረድኩትን አንድ ቀን ሳይረሳ
መጪውን ፈርጃለሁ ዓለም እስቲከሳ::
14.ቃሊቾችም ጠሉኝ ጠጅ ይጠጣል ብለው
ደብተራውም ጠላኝ ሹም ተጠጋው ብሎ
ባለዛሩም ጠላኝ ሰው ሄደበት ብሎ
ፋቅራውም ተጠጋኝ ምን ይፈርዳል ብሎ
እኒህን ችዬ ነው የሰጠኝ ጀሊሉ::
15. ጀግና አጼ ዮሐንስ ያበሶች ወንድም
የዛሬን ማርልኝ ያለ ዛሬ አይለምድም
በነገረ ሠሪ ሰው አይታረድም
እንዲህ ከሆነማ አንድ ስው አይተርፍም
እየደነገጡ ይሄዳሉ የትም::
16. ዓባይ በጣና ላይ መሄዱ ለምን ነው?
ትንሹ ሲያጠፋ ትልቁ ሊችል ነው፣
ቢያከፋም ቢያበጅም ዓባይ ማለፋ ነው
ሰውን በግዴታ የሚገዛው ማነው?
ከምክር በስተቀር የቀረው ከንቱ ነው::
17. ማረዱ ከፋ እንጅ ጀግንነት አያጣም
እስላም እሚያርድ እንጅ እሚወድ አይመጣም፣
የፈራህ ሰው ወጣ እኔ መልስ አላጣም
ይዘገያል እንጅ ሰው የጁን አያጣም
መተማ ከሄደ ተመልሶ አይመጣም::
18. አንተም እድሜህ አጭር ወይ ዘርህ አይገዛ
(ጎርፍ ደርሶ አይወስድም አለቅጥ ካልበዛ)
እንጨት ከደረቀ ቢቀቡት አይወዛ
(ሐበሻ ክፉ ነው አይምሰልህ ዋዛ)
መተማ እስቲጠራህ በብልሃት ግዛ::